የስርዓተ ፆታ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ሐገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሄደ

By emwa In News

05

Dec
2023

ህዳር 25፣ 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ፣ ማህበራችን ከ ፎጆ ሚዲያ  ጋር በመተበባበር  የስርዓተ ፆታ ፖሊሲ በመገናኛ ብዙሃን በሚል ርዕስ  ሃገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካዷል ፡፡

ይህ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን እና ሃላፊዎችን ያሳተፈ መድረክ የተካሄደው ማህበሩ የመንግስት፣ የግል እና የዲጂታል ሚዲያን አካቶ 16 መገናኛ ብዙሃን ላይ ባደረገው ጥናት የስርዓተ ፆታ ፖሊሲን በኤዲቶሪያል ፖሊሲው ላይ  አካቶ ያገኘው አንድ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ብቻ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

የጉባኤው ዋና አላማ በሚዲያው ዘርፍ የስርዓተ ፆታ ፖሊሲ ለእኩልነት እና ለፍትሃዊነት አስፈላጊ መሆኑን እና ለ ተቋማት እና ለተለያዩ አካላት ግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎ የሴቶችን የተሳትፎ ቁጥር በመጨመር ወደ አመራርነት ቦታ እንዲመጡ ማድርግ እና የስርዓተ ፆታ ፖሊሲን ለማዘጋጀት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ግብዓት ለመሰብሰብ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ መድረኩ የስርዓተ ፆታ ፖሊሲ አስፈላጊነት ፅንሠ ሃሳብ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሴቶችን ጥቃት ከመከላከል አኳያ የሌሎች ሃገር ተሞክሮዎች ለተሳታፊዎች ገለፃ የተካሄደበት ነበር፡፡  

በዚህ ጉባኤ የ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተቋማት ባለስልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ አንድም ዋና የስራ አስካያጅ ሴት እንደሌለ አንስተው ለዚህም ዋና ምክንያት በሚዲያ ተቋማት ውስጥ የስርዓተ ፆታ ፖሊሲን ተግባራዊ አለመደረጉን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶችን አንስተዋል እነዚህም ሴት ጋዜጠኞች ላይ በአቅም ግንባታ ዙሪያ እየተሰራ ያለው ስራ አነስተኛ መሆኑ፣ ሴቶች በሚዲያ ገብተው እንዲሰሩ የሚያደርጉ የቅጥር አሰራሮች አለመኖራች እና እንዲሁም ከገቡ በኋላ የሚኖርባቸው የቤተሰብ ጫናን ተቋቁመው እንዲሰሩ የሚያደርግ ድጋፍ አለመኖር ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ከፍ እንዲል የሴት ባለሙያዎችን ዝርዝር በማዘጋጀት ጭምር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ይህንንም  ለመቅረፍ ሴት ባለሙያዎችን ለማፍራት መመሪያዎችን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ስራዎችን ለመስራት እንደታቀደ ገልጸዋል፤ ከነዚህም አነዱ በቀጣይ በፈረንጆቹ 2024 ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የስርዓተ ፆታ ፖሊሲ እንዲኖራቸው ለማድረግ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

‘’ ማንኛውም የምናመጣቸው ፖሊሲዎች የሃገራችንን እሴት የሃገራችንን ሁለንተናዊ እውነት ማዕቀፍ ያካተቱ መሆን አለባቸው ከአንድ ችግር ለመውጣት ብለን ተስበን ወደ ሌላ ከሃገራችን ሁኔታ አንፃር የማይሆን ፣ የማይመጥን ሁኔታ ውስጥ እየተሳብን ከገባን ግን የተጀመሩ ስራዎች ሁሉ እየተሳቡ እንዲጠፉ ያደርጋል’’ አቶ መሃመድ እድሪስ ፡፡